Ad

Tuesday, December 25, 2018

ከዚህ ገጽ ተሳታፊ እህታችን የቀረበ ጥያቄ!

"ምዕመናን በቤተመቅደስ ሊኖራቸው የሚገባ ሥርዓት ቲኒሽ ቢብራራ❓

"ሥርዓተ ቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ወመቅደስ"


፦በቤተክርስቲያን ቅፅር ግቢ ገበያ ክልክል ነው። /ማቴ 21፡12 ዮሐ 2፡13-18 ፍትሀነገስት አንቀጽ 1/

፦በቤተክርስቲያን ቅፅር ግቢ ግብዣ ማድረግ፣መብላት፣መጠጣት ክልክል ነው። /የሎዶቅያ ሲኖዶስ (ዶቅ) 44 ፍ.ነገ 1/

፦ማንኛውም መብልም ሆነ መጠጥ ከቤተ መቅደስ 40 ክንድ(20 ሜትር) መራቅ አለበት! በመቅደሱ ሕብስቱና ወይኑ ብቻ ይፈተታልና። /ፍ.ነገ 1/

፦በታቦቱ ፊት ለመስገድ ወይም ለመፀለይ ወይም ለማስቀደስ ካልሆነ በቀር ማንም ወደ ቤተመቅደስ ገብቶ እንዲቀመጥ አይፈቀድም

፦ከካህን በስተቀር(ዲያቆናት፣ካህናት፣ቀሳውስት፣ጳጳሳት..) ከምዕመናን ወገን ወደ መቅደስ(ታቦቱ ያለበት) ገብቶ ሥጋ ወደሙን ሊቀበል(ሥጋ ወደሙን የሚያቀብሉ ካህናት ራሳቸው ሁሌም ከማቀበላቸው በፊት በመቅደስ ውስጥ ይቀበላሉ) ታቦቱን ሊጠጋ አይገባም /ፍ.ነገ 1፣ ቀኖና አብሉዲስ ፣ኢያሱ 3፡4/


፦ሴቶች ወደመቅደስ (ታቦቱ ያለበት) እንዲገቡና እንዲፀልዩ አልተፈቀደም። /የሎዶቅያ ሲኖዶስ(ዶቅ) 44፣ ፍ.ነገ 1/

፦ከቤተ ክርስቲያን አንዴ ለአገልግሎት ተመርጦ የገባውንና የተቀደሰውን ንዋየ ቅድሳት እንደገና ወደውጭ አውጥቶ መጠቀም አይገባም። /ፍ.ነገ 1፣ 1ቀለሚንጦስ (ረስጣ) 28/

፦ያላመኑ፣ ያልተጠመቁ፣ ተወግዘው የተለዩ ወደ ቤተክርስቲያን እንዳይገቡ ተከልክሏል። /ፍ.ነገ 1፣ ድድስቅሊያ (ድስቅ) 12/

፦ለፀሎትና ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል ወደ ቤተክርስቲያን በሚኬድባቸው ዕለታት፣ በጾምና በሰንበት፣ በበዓላት ወቅት ወንድና ሴት ግንኙነት ክልክል ነው። /ዘፀ 19፡15፣ 1ቆሮ 7፡5-7/ (ለባለትዳር ብቻ ነው! ያላገባማ በየትኛውም ጊዜ ከጋብቻ በፊት አይፈቀድም)

፦ነውር ያለበት ወደ ቤተክርስቲያን አይገባም። /ፍ.ነገ 13/

፦ሴት ልጅ ወር አበባዋ ሲመጣ ለ7 ቀን፣ ስትወልድ ወንድ ከወለደች እስከ 40 ቀን፣ ሴት ከወለደች እስከ 80 ቀን ወደ ቤተመቅደስ መግባት አይፈቀድም። (ዘሌ 12፡1__፣ ዘሌ 15፡19-28፣ ፍ.ነገ 6፣ ዘኒቂያ 29)

፦ወንድም ቢሆን ከአፉ ወይም ከአፍንጫው የሚወጣ ፈሳሽ ፣ነስር ሲኖርበት ወደ ቤተ መቅደስ አይገባም! ይህም ቤተመቅደሱን ስለሚያረክስ ወይም ለሌላ ሳይሆን በቤተ መቅደስ ውስጥ የክርስቶስ ደም ብቻ መፈተት ስላለበት ነው።

፦ወንድ ልጅ ሕልመ ሌሊት ከመታው(ህልመ ዝኔት ካየ(ስጋዊ ህልም ካየ) በዕለቱ ወደ ቤተ መቅደስ አይገባም። (ዘሌ 15፡2)

፦ጠዋትና ማታ ቤተክርስቲያን ለመሳለም መትጋት ያስፈልጋል። (ምሳ 8፡34)

፦ወደ ቤተክርስቲያን ሲገባ በቅፅረ ቤተክርስቲያን በር ላይ ሲደርሱ መሳለም ይገባል (መዝ 28፡2፣ መዝ 95፡9፣ ኤር 26፡2፣ ሕዝ 46፡3)

፦ወደ ቤተክርስቲያን (ቤተመቅደስ) ሲገቡ ጫማን አውልቆ ወገብን ታጥቆ አደግድጎ መግባት ይገባል። (ዘፀ 3፡5-6 ፣ ሐዋ 7፡33፣ ኢያሱ 5፡15፣ ፍ.ነገ 12)

፦በቤተክርስቲያን ውስጥ ተስለው የሚገኙ ቅዱሳን ሥዕላትን እጅ መንሳትና መስገድ ይገባል

፦በቤተክርስቲያን ውስጥ መሳቅ፣ ስለ ዓለማዊ ነገር መነጋገር ክልክል ነው። /ዮሐንስ አፈወርቅ 19፡32 ፤ 48፤6 አቡሊዲስ 7/

፦አጭር፣ ያደፈ፣ የሰውነት ቅርጽን የሚያሳይ ልብስ ለብሶ ወደ ቤተክርስቲያን መሔድ ፈጽሞ የተከለከለ ነው /ዘፀ 19፡10 ፣ ዮሐ.አፈ 4፡49-72/


ወስብሐት ለእግዚአብሔር! ይቆየን